ኢትዮጵያ በሰማያዊ እና ነጭ አጭር ዕይታ

(Read the English version here: Ethiopia in a Blue and White Nutshell)

 

አንዳንድ ጊዜ ባህል እንደ ሹፌር ጋቢና ወንበር ላይ ተቀምጦ እና በሹፌር ሊገለፅ ይችላል። ለምሳሌ በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ መካከል ያለውን የትራፊክ አደጋ እንመልከት።በየመንገዱ ጥግ የሚቆሙ መኪናዎች በማይበዙበት፤ የመንገድ መጥበብም እንደ እንግሊዝ በማያስቸግርበት በፈረንሳይ ውስጥ በመኪና አደጋ የሚሞተው ሰው ቁጥር ከእንግሊዝ በእጥፍ እንደሚበልጥ ባለፈው አረጋግጫለሁ። እነዚህ ሁለት ሀገሮች ከሞላ ጎደል አንድ አይነት መንገዶች እና የመኪና ሞዴሎች … ይጠቀማሉ።
በመረጃ የተደገፈ የአንትሮፖሎጂ ጥናቶችን በመደገፍ የሚታወቀው አሜሪካዊ አንትሮፖሎጂስት ክሊፎርድ ግሪትዝ በፃፈው the Balinese cock fight በተባለው አውራ ዶሮዎችን እንደቦክሰኛ መድረክ ላይ አውጥቶ ማደባደብ ላይ ያተኮረ የተደነቀ ወግ ላይ ማን ለየትኛው ወገን ያደላል ለምን ገንዘብ ያሲዛል ምን ያህል ገንዘብ የሚለውን በማጥናት ባህሪያቸው ከመጡበት ባህል ጋር ያለውን ዝምድና እንዲሁም ስለሰዎቹ ስነ ልቦናዊ ጥናት አድርጓል።
አንዳንድ ጊዜ የማሽከርከር ብቃት እና በቅንጦት እና በፍጥነት ማሽከርከር በቀጥታ ማክስ ዌበር ፕሮቴስታንት እና ካቶሊክ በሆኑ አገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ያስቀመጠበትን ጥናት ማየት ይበቃል። ፕሮቴስታንቶቹ በጥናቱ ጊዜ ደከም ያለ ኢኮኖሚ የነበራቸው የሰሜን ስካንዲኔቪያ ሀገሮች ሲሆኑ (ሁሉም ፕሮቴስታን ሃገሮች ናቸው) በጊዜው የተረጋጋ ኢኮኖሚ እና የስራ ዕድል ከነበራቸው PGIS (ፖርቱጋል፣ግሪክ፣ ኢጣሊያ እና ስፔን) እነዚህኞቹ ደግሞ ካቶሊኮች እና የዘመኑን ፈጣን ፌራሪዎች የሚነዱ ሲሆኑ የነበራቸውን ልዩነት አሳይቶናል።
ምናልባት ነገሩ የተደጋገመ ወይም አሰልቺ ሊሆን ይችላል። ግን አንድ ቦታ ልውሰዳችሁ። በዘመናዊቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ አዝናኝ ጉዞ። የሚያስፈልግዎ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ መሳፈር ብቻ። ማወቅ የሚገባዎ ደግሞ የት ነው? (yet no)ወራጅ (weradj) ስንት ነው? (sint no)እና መልስ ስጠኝ (mels setegn) የሚሉትን ቃላት ብቻ ነው። እንጀራ ከኢትዮጵያ ምግቦች ስም ጋር እንደሚነሳው ሁሉ ሚኒ ባስ ከአዲስ አበባ ጋር አብሮ ይነሳል። እጅግ በጣም ሲፈለጉ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ቦታ ይገኛሉ። ሁሉም ነዋሪ ለማለት በሚያስችል ሁኔታ ተጠቃሚያቸው ነው። ሚኒባሶችን ከእንጀራ የሚያመሳስላቸው አንድ ጉዳይም አለ እንጀራ አይን እንዳለው የሚኒባሶች ሰውነትም የተበሳሳ ከመሆኑም በላይ ውስጣቸው ሲገባ አፍ ውስጥ እንደ ሎሚ የሚቆመጥጥ ጣዕም ያሳድራሉ።
እንጀራን አንዳንድ ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ‘ባህላችን ነው’ ብለው እንደሚያስተዋውቁት ሚኒባሶችም በአጭሩ እየተቀየረ ያለው የከተሜ ባህላቸው መታወቂያ እየሆነ ነው። አንዱ ቅንጭብ ዕይታ ሌላውን ይወክላልና ትንሽ ደቂቃዎች በአንድ ሚኒ ባስ ውስጥ የጥንቷን እና ዘመናዊዋን ኢትዮጵያን እያየን እንጓዝ።

ጉዞው ከአራት ኪሎ ወደ ሜክሲኮ ነው እንበል
ተጠጋግቶ መቀመጥ ግን ደግሞ በጣም እንዳይጣበቁ ሆኖ የመቀመጥ ችሎታ፤ የኃላ መቀመጫው ላይ ለአራት ሲቀመጡ ጉልበትን በማይመች መልኩ አጠማዝዞ ከኋላ የመጣውን ተሳፋሪ ወደ ጥግ መስኮቱ አጠገብ (የሚኒባሱ አሪፍ ቦታ ነው) ለማስቀመጥ ያለው ጥረት። ወይም ደግሞ መስኮቱ ለፀሃይ በሚጋለጥበት ጊዜ እዚያ ላለመቀመጥ በተለይ ሴቶች ውበታቸውን ፀሃይ እንዳይጎዳው የሚያደርጉት መከላከል። እጅግ አስደሳቹ የሰዉ እርስ በርስ መከባበር በተለይ ደግሞ ለአረጋዊያን እና ለእርጉዞች የሚደረገው ቀና ትብብር የኢትዮጵያ ሚኒባሶች የሚታወቁባቸው ባህሪያት ናቸው።
ይህ ታላቅ ስነምግባር በሁሉም ዘንድ የተለመደና የዳበረ አንዳንድ ጊዜ እንደውም የሀገሪቱ መታወቂያ ጭምር ይመስላል። የታክሲውን በር የሚከብቡ የኔቢጤዎች ደግሞ አሉ ተሳፋሪ እንዲያያቸው ነው መቼስ… እኔ እራሴ ለታክሲ አሸከርካሪዎች ማህበር የድርሻቸውን በፐርሰንት እንደሚከፍሉ እጠረጥራለሁ። ግን ጥርጣሬ ብቻ ነው። ቆይ በየትኛው ዓለም ነው ሰዎች ለየኔቢጤ ስሙኒ ሰጥተው ለአምስት እና አስር ሳንቲም መልስ ቆመው ሲከራከሩ የምታዩት?
ከዚያ ደግሞ ወያላ (weyala) አለ። አብዛኛውን ጊዜ ታማኞች እና ትክክለኛውን መልስ ሳንቲም ድረስ ቆጥረው በትክክል የሚሰጡ። ለማንኛውም ግን ወያላ መባልን ሳይሆን ረዳት (redate) አጋዥ እንደማለት ነው መባልን ይመርጣሉ።ከአራት ኪሎ ሜክሲኮ ሁለት ከሰማኒያ ከሆነ ሶስት ብር ተቀብሎ ሃያ ሳንቲም ይመልሳል። በኢትዮጵያ ውስጥ አካፋን አካፋ አትለውም ወያላንም ወያላ አትለውም። ይህ አጠቃላይ ህግ ሲሆን ተሳስተው ካመለጥዎ ግን እንዳልሰማ ይታለፍልዎታል።
ይኸው ወያላ ተብሎ መጠራት የሌለበት ሰው በብዛት ታክሲ ማቆሚያ አካባቢ ከሚቆሙ ኮስታራ ልጆች ጋር ዱላ ቀረሽ የቃላት ፍልሚያ ያደርጋል። እነዚህን ምን ተብለው ስም እንደወጣላቸው አላውቅም ግን ማንም በዚያ ስም እንደማይጠራቸው እርግጠኛ ነኝ ። ኸረ ባንዲራዬን አውርጃለሁ! ከወያላ እንዲሁም ከሹፌር ተጣሉ፣ ተሳፋሪ ፊት የመኪናውን በር ዝጉ፣ መጥፎ ቃላትም ተለዋወጡ።አያገባኝም። ለዚህ ለፈጠሩት እሰጥ አገባ እና ችግር ደግሞ የጠየቅኳቸው ሰዎች ሁሉ ሊገልፁልኝ ባልቻሉት ሚስጥራዊ ጥበብ ገንዘብ ይቀበሉበታል። እንደገና ወደ ኢትዮጵያዊያን የስራ ባህል ስንገባ አሰራራቸው እንደ ሚኒባሶች ነው። በማንኛውም የስራ መስክ ከሚያስፈልገው የሰው ኃይል በላይ በማስገባት ከቻልክ ስራውን በጣም ውስብስብ አድርገው ተጨማሪም አላስፈላጊ ወጪዎች ፍጠር።
እንዲህም ሆኖ ወያላዎች እነዚህኑ የሚጣሏቸውን ልጆች የመድረሻ ቦታቸውን ሲያስጠሯቸው፤ እናም ተሳፋሪዎችን ወደ ትክክለኛው መኪና ሲመሩላቸው አያለሁ። በዚህ መንገድም ቢሆን ወያላዎቹን እየጠቀሟቸው እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም ምክንያቱም ወያላዎቹ 1. አማራጭ የላቸውም (እነዚህ የሚኒባስ ተቆጣጣሪዎች ባሉበት ቦታ ትንሽ ጠርተው ለወያላ እና ለሹፌሩ ቢያንስ የሚከፈለኝ ሰርቼ ነው ለማለት) ወይም 2. ወያላው ትንሽ አረፍ ለማለት ጊዜ ስለሚሰጠው፤ እሱም በተራው ደግሞ ከሱ በታች ላለው የስራ ዘርፍ ሰራተኛ ከፍሎ ለማሰራት ይሆናል። እንደገና ደግሞ ከሚኒባስና ኢትዮጵያ ዙሪያ ሳንወጣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የአንድ ከስሩ ሊወጣ የማይፈልገው ወደ ሌላ አቅጣጫ ዘወር የማይልበት የግሉ ስራ አለው። አንድ ሰው ሁለት ሦስት ስራ ሊሰራ አይችልም እንዴ? ይህ ጥያቄ በመነሳቱ ይቅርታ።
የሚኒባሳችን ተሳፋሪዎች ዓይነታቸው ብዙ ነው፡ ግን የሚያስቸግሩ ዓይነት ሰዎች አይደሉም። ጋቢና ሁለት አፍላ ወጣት የቦሌ ቆነጃጅት ተቀምጠዋል። በአይፎኖቻቸው ከማናገር አረፍ ሲሉ እርስ በርሳቸው በአማርኛ እና በአለማቀፍኛ ያወራሉ። በኩራት መንፈስ ነው የሚያወሩት ምናልባትም የጠጡት የካልዲስ ቡና ስሜታቸውን ከፍ አድርጎት ይሆናል የለበሱት ሚኒ ስከርት እንደዚያው ከፍ ያለ ነው። ከሱ ቀጥሎ ባለው ወንበር የአራት ኪሎውን አቡን ጎብኝተው የሚመለሱ ቄስ ወደ ሰንጋተራ ሱቁ ከሚቸኩለው ሙስሊም ጎን ተቀምጠዋል። ጎን ለጎን ተነካክተው ሁለቱም ዘና ብለው ተቀምጠዋል። ከነሱ ኃላ ወንበሩ ላይ በተቀመጠበት የሚቅበጠበጥ ቀጭን ከረባት ያደረገና በለጭለጭ ያለ አለባበስ የለበሰ ሰው በሞባይሉ ባለስልጣን እንደሆነ እና ትዕዛዝ የሚሰጥ መሆኑን ሁሉም እንዲያውቅለት አድርጎ ያወራል።ከጎኑ ነጭ ነጠላ የለበሰች ሴት ተቀምጣለች ባትናገረውም በዚህ ጉረኛ ሰው እና የስልክ ስነምግባር ከንፈሯን ሾል ትንሽ ደግሞ ጋደድ አድርጋ ስሜቷን ፊቷ ላይ ስላዋለች።ከአሜሪካ የተመለሰ ወንድማቸውን ሊጠይቁ አዲስ አበባ የመጡ ገበሬ የበርኖስ ኮፍያ ሰማያዊ የጨርቅ ሱሪ በተመሳሳይ ጨርቅ የተሰራ ኮት የለበሱ ሲሆን የፊታቸው እና የእጆቻቸው መስመሮች ብዙ ናቸው። ከጎናቸው የተቀመጠችው ሚስታቸው ፊቷ ላይ የእርሻ ቦታ ላይ ከመስራት የተነሳ ደመቅ ያለ ማዲያት አለባት እንዲሁም ቅመምቅመም የሚሸት ቅቤ ተቀብታለች። ካሉት 12 መቀመጫዎች 8ቱ የተያዙት አይናቸው የሚያበራ ተስፋ የሚታይባቸው ወጣቶች ነው ።ሃሳባቸው የተያዘው በሞባይል ስልክ፣ በምርጥ ልብሶች እና በስራ። በቤተ ክርስቲያን አጠገብ ሲያልፉ አንዳንዶቹ እያማተቡ ተሳለሙ። ወዲያው ግን ስልካቸውን ወደ መጎርጎር ገቡ። በጋቢ እና በበርኖስ የተጀቦነው ከበቂ በታች ከለበሰችው ጋር በጓደኝነት መንፈስ እያወሩ የባህላዊ ንቅሳት እየተረሳ አልፎ አልፎ በድሮ ሴቶች ላይ ብቻ እየታየ። ቄሱ ቀሚሳቸውን ከጎን በኩል ሳብ አደረጉት ሙስሊሙ ነጋዴ እንዳይጠብባቸው በደንብ ፈቀቅ አለ። የቦሌዎቹ ቆነጃጅት በየአይፎናቸው ማውራታቸውን የገበሬው ሚስትም አካባቢውን በቅቤ ሽታ ማወዷን ቀጥለዋል። በዚህ ሚኒባስ ዘመናዊነት እና የ2000 ዓመት ስልጣኔ ትከሻ ለትከሻ ምናልባትም ክንድ ለክንድ ሊሆን ይችላል ይነካካሉ። በመጨረሻው መቀመጫ አራት ሰዎች ተቀምጠዋል። ወጣቶቹ ወንዶች ሴቶቹን ያያሉ ሴቶቹም እንዲሁ ወንዶቹን በሚስጥር ይተያያሉ ሚኒባስ ኢትዮጵያም እንዲሁ እየሄደች ነው።
ሹፌሮቹስ ቢሆኑ? አሁን አሁን ሹፌሮች ቀበቶ እንዲያደርጉ ተደርጓል። በዋነኝነት። ቆይ ቀረብ ብላችሁ ስትመለከቱት ግማሽ የሚሆኑት ለአነዳዳቸው የተሰጠ ሜዳሊያ ይመስል የውሸት ቀበቶዎችን እንደሚያስሩ ትመለከታላችሁ በትክክል አያስሯቸውም። ደግሞስ ሹፌሩ ቀበቶ ማሰሩ የግድ ከሆነ ጋቢና የሚቀመጡት ሁለት ተሳፋሪዎችስ ለምን አያስሩም? ምክንያቱ አይታወቅም። ሹፌሮቹን ብትጠይቋቸው የሚመልሱት መልስ “ከድሮም ቢሆን እንዲሁ ነው” የሚል ነው። አንድ ሁለት የታክሲ ሹፌሮችን ይህ ህግ በአክሱም ዘመን የወጣ ሳይሆን አይቀርም የሚባለው እውነት ነው? ብዬ ጠይቄ ነበር። በፍፁም ያን ያህል ዕድሜ እንደሌለው የነገሩኝ ሲሆን ምናልባት በሚንሊክ ጊዜ ሳይሆን እንደማይቀር ጠቁመውኛል።
ይህ የጋቢና ተሳፋሪን ትቶ አሽከርካሪዎችን ብቻ ቀበቶ የሚያሳስር (ግማሽ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ የታክሲ ሹፌሮች ባይጠቀሙበትም) አዲስ ህግ (በነገራችን ላይ ትራፊክ ፖሊሶች እውነታውን እያወቁም ቢሆን ሹፌር የውሸት ቀበቶውን ጨዋታ ካልተጫወተ ማስቆማቸው አይቀርም) ሌላው የኢትዮጵያ ሚኒባሶች መገለጫ ፀባይ ነው። ሁልጊዜ ህግን እና ስምምነቶችን ላይ ላዩን አክብር። ቅርፁ ብቻ እንጂ ይዘቱ ዋጋ የለውም።
ሹፌር የራሱን ቀበቶ እንደ ኒሻን ደረቱ ላይ ካሳየ ለሌላው ነገር እምብዛም አይጨነቅም። እያወራሁ ያለሁት አውቀው እንዳይሰራ የሚያደርጉትን የጋቢና መስታወት ነው። ያንን መስኮት መክፈት ከፈጣሪ የተከለከለ ያህል ነው። ሹፌሩን እንዲከፈት የጠየቁት እንደሆን በብርድ ታስገድለኛለህ! ብሎ ይፈነዳል። ይህንንም ሲያደርግ ፊቱን ከመንገዱ ወደ እርሶ ለ20ሰከንድ ያህል መልሶ፣ ጉልበቱ መካከል ያስቀመጠውን የኮካ ጠርሙስ፣ በግራ እጁ ውስጥ ደብቆ የያዘው ስልክ ላይ የጀመረውን ወሬ እና በኪሱ ውስጥ የሚያፍተለትለውንውን የጫት ቀንበጥ ሁሉ ለአፍታ ረስቶ ነው። እርግጥ ነው በጥንቃቄ ለመጓዝ ከፈለጉ አንድ ቀላል ዘዴ አለ። በዕድሜያቸው ገፋ ያሉ ሹፌሮችን መምረጥ። ለመሞት የቀረቡ ስለሆኑ ለህይወታቸውም ሆነ ለተሳፋሪ ህይወት ቅድሚያ ይሰጣሉ። የ18 ዓመቶቹ ሹፌሮች ግን በመኪና መሃል ይሽሎከሎካሉ፣ ከትራፊክ ዕይታ ለማምለጥ ይሞክራሉ ወይም ከመሰሎቻቸው ጋራ ይፎካከራሉ።
እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ስራ መሰጠት ያለበት ለሴቶች እና ለአረጋዊያን ነበር። ይህ ቀላል እርምጃ የትራፊክ አደጋዎችን በ80% ለመቀነስ ይችላል። ሚኒ ባስ ውስጥ ያለ ትህትና እና መከባበር በተቃራኒው ደግሞ ከውጪ ያለው መሰዳደብ እና ጭቅጭቅ ወይም ቢያንስ ሹፌር እና ተሳፋሪን አለማክበር እና ሌላም ብዙ የሚታይ ነገር አለ – ዶናልድ ሌቪንን የታወቀ መፅሃፍ ‘wax and gold’ ወይም ሰምና ወርቅ የተባለ መፅሀፉን መንዝ ድረስ ሄዶ ያፃፈው።
ግን የመኪና አደጋዎቹ ውይ… ውይ። በየቀኑ በኢትዮጵያ አውራ መንገዶች ላይ የምናያቸውን ተወት እናድርግና የትራፊክ አደባባዮች ላይ እናተኩር። ለመሆኑ ሹፌሮች መኪናዎቻቸውን አደባባይ ላይ ወይም የትራፊክ መንገድ መሃል የሚያቆሙት እና መንገዱን የሚያጨናንቁት በምን ምክንያት ይሆን? ከትራፊክ መጨናቅ በተጨማሪም ለአደጋ ያጋልጣል። ምክንያቱ ምን መሰላችሁ? የትራፊክ ፖሊስ መጥቶ አደጋው የደረሰበትን ቦታ በቾክ አስምሮ ሁለቱንም ባለመኪናዎች እስኪገላግላቸው ድረስ ለመጠበቅ። ይህ እርስ በርስ አለመተማመን እና መካሰስን መፍራት የኢትዮጵያን ሚኒባሶች በቀጠሮ እና በስራ ሰዓት የልብ አድርስ እንዳይሆኑ እንቅፋት ሆኗል።
ሌላው በጣም የተመቸኝ ነገር ምንድነው? በቤተክርስቲያን አካባቢ ሲያልፉ በፍጥነት መሳለም። ሚኒባሱ እንደወፍ በሚበር ፍጥነቱ በቤተክርስቲያን አካባቢ ካለፈ ከጎን የተቀመጠውን ሰው ላለመጎሸም ጥረት አድርጎ በትዕምርተ መስቀል ተሳልሞ ራስን ትንሽ ዝቅ ማድረግ። ምን አይነት ፋሽን ነው? እኔ እራሴ ወደ ሚኒባሶች ስገባ መጀመሪያ ነው የማማትበው። ይህን ማድረጌ በጉዞ ወቅት የሰላም መንፈስ ይሰጠኛል። እንደዚህ ዓይነቱ ልታይ ባይ ሀይማኖተኝነት እና “እምነቴ ከአደጋ ሁሉ ይጠብቀኛል” የሚል ዕምነት የሚኒባሶች ሌላው ገፅታ ሲሆን በኦርቶዶክስ አማኙ ምስል፣ በሙስሊሙ ቅዱስ ቁርዓን ጥቅሶች እና በያማሃ ኪቦርድ በታጀቡ የጴንጤ መዝሙሮች ይታጀባሉ።
ጉዞው በራሱ አውሮፕላን አኮብኩቦ ሊነሳ ሲል ያለውን የፍርሃት ስሜት ያስታውሳል።
ከአራት ኪሎ በሜክሲኮ መስመር ሲሄዱ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ሲደርሱ ደህንነትዎን ከሞላ ጎደል ያረጋግጣሉ። በጣም አደገኛው ቦታ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርን አለፍ እንዳልን ያለው ቦታ ስለሆነ ማለት ነው። ከውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ያለው ባተሌ የመንገድ ማቋረጫ ላይ ስንደርስ ጋቢና ከተቀመጥኩ ለሹፌሩ በቀስታ “አደራህን እንደተለመደው ደግሞ አየር ላይ እንዳታበረን!” እለዋለሁ። በሃሳቤ ግን ለአንዲት ሴኮንድ ትኩረቱን ቢስት ምን ሊያጋጥመን እንደሚችል አውጠነጥናለሁ። መስቀለኛ መንገዱን እንዳለፈ በእዮቤልዩ ቤተመንግስት ፊት ለፊት የምትገኝ አበጥ ያለች ቦታ አለች። ሾፌሩ በፍጥነት እየነዳ ከሆነ መስቀል አደባባይ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የተለጠፈውን ትልቅ የኢትዮጵያ አየር መንገድ “ድሪም ላይነር” አውሮፕላን በርረው የሚገናኙት ይመስላል። ሽ…….ው
መስቀል አደባባይ ከደረሱ በኃላ – እስጢፋኖስን መሳለም እንዳለ ሆኖ- አዲስ ሩጫ ይጀመራል። ብዙውን ጊዜ መስቀል አደባባይ ላይ ያለው የትራፊክ መብራት ስለማይሰራ ወደ ስቴድየም ቀድሞ ለመድረስ የፍጥነት እና የመሰናክል ዓይነት ውድድር በሚኒባሶች መካከል ለአጭር ጊዜ ይደረጋል። ሆ ሆ በመስቀል አደባባይ መሃል መሞት አልፈልግም፡፡ ወደ ስቴድየም ከዚያም ወደ ሜክሲኮ። ለማንኛውም እግረኞች ተጠንቀቁ።
[ተጨማሪ ለመንገደኞች የምጨምረው በተለይ በብዛት የአሽከርካሪ ዘለፋ ከደረሰባችሁ። ዜብራ መንገድ ዋነኛ ጥቅሙ የተናደደ አሽከርካሪ “አንተንስ መግጨት ነበር” ብሎ እግረኛ በሚያደርገው ጥፋት ምሬቱን መግለፅ ማስቻሉ ነው። ምክንያቱም ደግሞ እግረኞች መንገድ ሲያቋርጡ 45 ዲግሪ ወይም የጎንዮሽ እያዩ ስለሚገቡ ነው። ሁለት ዓይነት እግረኞች አሉ። ሁለቱም ደግሞ ወንዶችን ይመለከታሉ የመጀመሪያዎቹ ሚኒባስ *ቶሬሮ ሲባሉ በቀጥታ ወደ ሹፌሩ ይመለከታሉ ሾፌሩንም ‘አይተኸኛል’ የሚል ማስጠንቀቂያ በአይናቸው ከሰጡት በኃላ የሚያመጣውን ያምጣ ብለው ፊታቸውን በተቃራኒው አቅጣጫ አዙረው በድፍረት ወደ መንገዱ የሚገቡ ናቸው። ሁለተኞቹ ደግሞ የመኪና መምጣትን እያወቁ ወደ መኪናው የማይዞሩ ናቸው። እናዚህኞቹን ደግሞ ሚኒባስ *ካሚካዝ እንላቸዋለን]አንዳንድ ጊዜ በኢትዮጵያዊ ሚኒባስኛ ኩራት እና ትዕቢትን ለይቶ መግለፅ ይከብዳል መሰለኝ። ምን ለማለት እችላለሁ? በየዕለቱ የትራፊክ አደጋ ክፉኛ ሰለባዎች እግረኞች ቢሆኑም በከፍተኛ የጥንቃቄ ጉድለት ለሚፈፀም አደጋ የሚሆን ሀዘኔታ ማሳየት ግን ይከብዳል።
ታዲያ ኢትዮጵያን በአንድ ሰማያዊ እና ነጭ ሚኒባስ ውስጥ እያጠቃለልኳት ነው? ኢትዮጵያዊያን ክብ የሰርዶ እንጀራቸውን እንደዘበት ባህላችን ነው ሲሉ ከዚያ ያነሰ ወይም በላይ ማለታቸው ሊሆን ይችላል። በተመሳሳዩም እኔም ግማሹ በቀልድ ቢሞላም የኢትዮጵያውያንን ማህበረሰብ ለመቃኘት በትንሽ ገንዘብ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ተሳፈሩ ነው የምላችሁ። እነዚያ የፈረሰ ላቦራቶሪ የመሰሉ ሚኒባሶች ውስጥ የማህበረሰቡን ውስጥ እና ማንነት ለማየት ትችላላችሁ። እንዲህም ስል ከተናገርኩት ያነሰ ወይም የበዛ ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ኢትዮጵያ በሰማያዊ እና ነጭ አጭር ዕይታ ‘ባህላችን’ ወራጅ!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

*ቶሬሮ ማለት ከደለቡ በሬዎች ጋር በአንድ እግሩ በመቆም ተጋፍጦ ትርኢት የሚያሳይ ደፋር ነው።
*ካሚካዞች በአንደኛው ዓለም ጦርነት የነበሩ የጃፓን ፓይለቶች ሲሆኑ የሚሰለጥኑትም ዒላማ ከተረደጉ መርከቦች እና የጦር ሰፈሮች ጋር ቦንቦችን በታጠቁ አውሮፕላኖች መጋጨት እና መፈንዳት ነው።

 

 

(Translation by Samuel Asfaw)